Print this page
Rate this item
(0 votes)

ከሙያ ማኅበራት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም.

የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ያለውን ሀገራዊ ምላሽ /National response/ ለማገዝ የጤና ሙያ ማኅበራት የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትዮጵያ አሳሳቢ እና ዋነኛ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር በተለያዩ አካላት በተለይም በመንግስትና በሙያ ማህበራት  ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ ሲቪል የማሕበረሰብ ድርጅቶች አካል የሆኑት የጤና ሙያ ማሕበራት ተቀናጅተው ህብረተሰቡ ለበሽታው እንዳይጋለጥ ሳይንሳዊ /scientific/ እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ /evidence based/ በሆነ መንገድ መንግስት እየወሰደ ያለዉን የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃ በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡

ለአብነት ያህል ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡ እንዲሁም የበሽታውን ምንነት እና መከላከያ መንገዶችን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ልዩ ልዩ መልዕክቶችን በማሳተም እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ቫይረሱ በሌሎች አገሮች እያደረሰ ካለው አስከፊ ቀውስ በመነሳት በጋራ እየሰራ የሚገኘዉ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አካል የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዉን በተሻለ ሁኔታ ለማቀናጀትና የተለያዩ አካላትንም ድርሻ ለመጠቆም ይህ መግለጫ ተዘጋጅቷል::

ከሙያ ማህበራት የሚጠበቅብን ተግባራት

  1. የሙያ ማህበራት አባላትና መላዉ ሕብረተሰብ ከኮቪድ-19 በሽታ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ተአማኒ ከሆኑ የመረጃ ምንጮች በማግኘት እና በተግባር ላይ በማዋል ከበሽታው ራሳቸዉን እንዲከላከሉ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርብ እንሰራለን፥
  2. የሙያ ማህበራት አባላትና መላዉ ሕብረተሰብ ጠቀሜታው በውል ባልተረጋገጠ እና በጠንካራ መረጃ ባልተደገፈ የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ መንገድ ተዘናግቶ ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ደረጃዉን የጠበቀ መረጃ ለመንግስታዊና ለግል የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም ለማህበራዊ ድረ ገጾች በማስተላለፍ የጤና ሚኒስቴርን እንረዳለን እንዲሁም እናስተምራለን፤
  3. በተለያዩ ምክንያት የመረጃ ምንጫቸው ውስን ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች /የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ/ ተስማሚ የሆኑ የኮቪድ-19 በሽታ ወቅታዊ መረጃዎች እንዲደርሱ ከሚመለከታችው አካላት ጋር መተባበር እንሰራለን፤
  4. በተለይ በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መረጃዎች በተቻለ መጠን የሕብረተሰባችንን ሰፊ የእውቀት እና የአመለካከት ልዩነቶች ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ እናግዛለን፤
  5. በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ላለው ያልተገባ እና ምክንያት የሌለው ከልክ ያለፈ ፍርሃት ብሎም መረበሽ /panic and fear/ በቂ እና ተከታታይ ምላሽ በመስጠት ሕብረተሰቡን ማረጋጋት እና በዋና ዋና የመከላከያ መንገዶች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ እንመክራለን፤
  6. ከመንግስት /ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በሕክምና አሰጣጥ /clinical management/፥ የበሽታ አምጪ ተሃዋሲያንን መከላከልና ቁጥጥር /infection prevention and control/፥ የተጋላጭነት ተግባቦት /risk communication/፤ በመረጃ አያያዝና ጥንቅር ረገድ መንግስትን እንረዳለን፤
  7. የጤና ባለሞያዎች በማንኛውም ጊዜ ራሳቸውን የመከላከል በቂ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ እናሳስባለን::

 

ከመንግስት የሚጠበቁ ተግባራት

  • መንግስት በጤና የሰው ሃብት ልማት ረገድ ከሙያ ማህበራት ጋር በመቀናጀት እያደረገ ያለውን ፈጣን እና የድንገተኛ ጊዜ ምላሽ በተመሳሳይ መልኩ በሕብረተሰብ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ አጠናክሮ መቀጠል፤
  • ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና ባለሙያዎች የጀርባ አጥንት እንደመሆናቸዉ መንግስት የጤና ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት እንዲሁም ደህንነታቸዉን ለመጠበቅ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ፤ ከዚህም ባሻገር በቂ በጀት በመመደብ አስፈላጊ የህክምና ግብአቶችን በተለይም Personal Protective Materials እንዲሟላ ጥረት ማድረግ
  • ቫይረሱን መከላከልና መቆጣጠር የሁሉም የመንግስት፡ መንግስታዊና የግል ተቋማት፡ እንዲሁም የማህበረሰቡ ሃላፊነት ስለሆነ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ጥብቅ አቅጣጫ ማስቀመጥ፤
  • ከሌሎች አገሮች የተገኙ ተሞክሮዎችን በመተግበር የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዉን ማፋጠን ያስፈልጋል፤
  • ተኣማኒነቱ የተሟላ መረጃን ለማህበረሰቡ በተለያዩ ቋንቋዎች በተከታታይ ማቅረብ፤
  • የሙያ ማህበራት አባላቶችን በማስተባበር ይህን ወረርሽኝ ሊገታ በሚያስችሉ ሁሉም ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለህብረተሰቡ ጤና ዘብ መቆም፤
  • ወደ ክልሎች እንዳይዛመት አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ናቸው፡፡

ከማኅበረሰቡ የሚጠበቁ ተግባራት

ይህ ቫይረስ ጎሳ፣ ሐይማኖት፣ ክልል፤ ሃብት መጠን፣ የትምህርት ደረጃ፣ የቆዳ ቀለም፣ ጾታ እና እድሜ ሳይለይ የሰውን ልጅ የሚያጠቃ ቢሆንም በማኅበረሰብ ጤና ላይ ያተኮረ የመከላከል ስራ በመስራት መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ

  • ከጤና ባለሞያዎች ፣ የሙያ ማኅበራትና በመገናኛ ብዙሃን በኩል የሚሰጡ መረጃዎችን ብቻ መከታተል፤
  • እስካሁን ድረስ ቫይረሱን የሚያድንም ሆነ የሚከላከል ምንም ዓይነት መድኃኒት ያልተገኘ በመሆኑ ማኅበረሰቡ በተሳሳተ መንገድ ለተጨማሪ ችግር እንዳይዳረግ መጠንቀቅ ፤
  • እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ቫይረሱ በንክኪ ብቻ የሚተላለፍ በመሆኑ የሚሰጡትን ትምህርቶች በአግባቡ መተግበር ናቸው:: ስለዚህ
  • እጆችን በሳሙና በአግባቡ ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣
  • ከመጨባበጥ፣ መተቃቀፍ እና መሳሳም መታቀብ፣
  • ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ፤ ተራርቆ መቀመጥ፣ ታረርቆ መሰለፍ
  • ሰዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች አለመሄድ
  • ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱና ትኩሳት ካላቸው ሰዎች ቢያንስ ሁለት እርምጃ ያህል መራቅ፣
  • በሚያስነጥሱና በሚያስሉበት ወቅት ክንድን በማጠፍ አፍና አፍንጫዬን መሸፈን
  • አስገገዳጅ ህኔታ ከሌለ ከጉዞ መታቀብና በቤት መቆየት
  • አይኖችን፣ አፍንጫንና አፍን ከመንካት መቆጠብ
  • ያልበሰሉ የእንስሳትና የአሳ ምግቦችን ከመመገብ መታቀብ
  • ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት (ኮቪድ -19) አጋላጭ ሁኔታዎች ሲኖረን እና ምልክት ከታየብን፤ እንዲሁም ምልክቶችን በሌሎች ላይ ካየን በአስቸኳይ 8335 ወይም 952 በመደወል የህክምና እርዳታ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
    • ኅብረተሰቡ በመንግስት በኩል የሚሰጡ እና የሚወጡ ወቅታዊ የሆኑ የኮቪድ-19 በሽታ መረጃዎችን በመከታተልና በመተግበር ራሱን እና ቤተሰቡን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

 

ከሚዲያ አካላት የሚጠበቁ ተግባራት

  • ሁሉም የሚዲያ አካላት ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማዳረስ፤
  • ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ ሰፊ የአየር ሰዓት ሽፋን በመስጠት ወቅታዊ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማድረስ፤
  • የሚዲያ ባለሙያዎች ስለቫይረሱ አግባብ ያለውን ስልጠና በመውሰድ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ፤
  • የተሳሳቱ መረጃዎች በልዩ ልዩ መንገድ በሚተላለፍበት ወቅት የማስተካከያ እርምጃ መስጠት፤

የሙያ ማኅበራቱ ስም ዝርዝር

  1. የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር
  2. የኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር
  3. የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር
  4. የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መኮንኖች ማኅበር
  5. የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና ባለሞያዎች ማኅበር
  6. የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር
  7. የኢትዮጵያ ሳይኮሎጂ ባለሞያዎች ማኅበር
  8. የኢትዮጵያ ህክምና ላቦራቶሪ ማኅበር
  9. የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር

Latest from Super User