Who's Online

We have 204 guests and no members online

Rate this item
(2 votes)

የመጀመሪያ ዲግሪ የጤና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በመጪው ዓመት በሶስት የጤና መስኮች ለመጀመሪያ ዲግሪ የጤና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ  ምዘና መስጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ወንድምአገኝ እንቢአለ እንደተናገሩት፥ በመጀመሪያ ዲግሪ ለተመረቁ የጤና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ለመስጠት ቅድመ ዝግጀት ተጠናቋል።

የብቃት ማረጋገጫ ምዘናው በህክምና የሚፈጠሩ ስህተቶችን በማስቀረት ለህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመሰጠት ያስችላልም ነው ያሉት ።

ምዘናው በአዋላጅ ነርስ፣ ሰመመን ሰጪ እና ህክምና ሳይንስ፥ በያዝነው አመት የጤናውን መስክ በሚቀላቀሉ 2 ሺህ 120 ባለሙያዎች የሚጀመር ሲሆን ፥ በቀጣይ አመት በሁሉም የጤና ዘርፎች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ምዘናውን የሚሰጠው ከጤና ሙያ ማህበራትና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በመቀናጀት ሲሆን፥ ተመዛኝ ተማሪዎችም ምዘናውን የሚወስዱት ትምህርታቸውን በተከታተሉበት ተቋማት እንደሚሆን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በቀጣይ በሃገሪቱ ውሰጥ ከተለያዩ የጤና ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ወደ ሰራ ከመሰማራታቸው በፊት ምዘናውን እንዲወስዱ ይደረጋልም ብለዋል።

ምዘናውን የማያልፉ ባለሙያዎች በግልም ይሁን በመንግስት የጤና ተቋማት መስራት እንደማይችሉም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ደረጃ ኤጀንሲ በበኩሉ፥ በመጀመሪያ ዲግሪ በተወሰኑ የትምህርት ዘርፍ የሚሰጠውን  ምዘና በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጀት መጠናቀቁን ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ተሾመ እንዳሉት፥ በሁሉም የትምህርት መስኮች የሚሰጠው ምዘና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በከፍተኛ ደረጃ እገዛ ይኖረዋል።

Source http://fanabc.com