Who's Online

We have 306 guests and no members online

Rate this item
(0 votes)

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የአካላዊ እና ማኅበራዊ መራራቅ ትግበራ እጅግ አናሳና በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ትኩረት ሰጥቶ እንዲተገብር የሙያ ማኅበራት ጥሪ አቀረቡ።

 

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መኮንኖች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና ባለሞያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሳይኮሎጂ ባለሞያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ህክምና ላቦራቶሪ ማኅበር እና የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር በቅንጅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረጉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ማኅበራቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ በተለይም የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ በግብይት ስርአቱ ወቅት በአካላዊ መራራቅ ትግበራ ረገድ የታየው ቸልታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በማውሳት በቤት ውስጥ መቆየትና የጉዞ ክልከላ ህጎች በተግባር እንዲተረጎሙ ጠይቀዋል። 

አያይዘውም የጤና ባለሙያዎችን የግል ደህንንት መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረትን ለመቅረፍ መንግስት በአገር ውስጥ በማምረትም ሆነ በፈጣን የግዥ ሒደት  የቁሳቁሶች አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲጨምር አሳስበዋል፡፡

እንደማኅበራቱ መግለጫ በየእለቱ ምርመራ እየተደረገላችው ያሉት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር የናሙና ምርመራ አቅርቦቱን በማሳደግ በቀን ቢያንስ 5,000 ለሚያህሉ ሰዎች ምርመራ እንዲያካሂድ መክረዋል።

የበሽታ አምጪ ተሃዋሲያንን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጁ መመሪያዎችን የጤና ባለሙያዎች በሁሉም ቦታና ጊዜ በአግባቡና በጥብቅ እንዲተገብሩ አበክረው ያሳሰቡ ሲሆን፤ በየብስና በአየር ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች በበሽታ አምጭ ተሃዋሲያን መከላከልና ቁጥጥር መርሆች መሰረት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠይቀው፤ ለዚህም ትግበራ የቴክኒክ እገዛ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም የሚዲያ አካላት ተአማኒነቱ የተረጋገጠ መረጃ በማቅረብና በሽታውን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ረገድ አርአያ መሆን እንዳለባቸው የሙያ ማኅበራቱ  አሳስበዋል፡፡