ግንቦት 13/2017 ዓ.ም
“ተከታታይ እና ዘላቂ መፍትሄ ላይ ያነጣጠረ የባለድርሻ አካላት ምክክር ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው”

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ከተመሰረተበት ከ 1981 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን የጤና ልማትና ሥርዓት መሻሻል ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ከሃገርም አልፎ በአህጉራችን አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትና መልካም ገፅታ ያለው ስመጥር የሙያ ማህበር ነው። ማህበራችን የተቋቋመባቸዉ በርካታ አላማዎች ዉስጥ አንዱ የአባላቱን መብትና ጥቅም ማስከበር ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ዉይይት ሲያደርግና በጤናዉ ስርዓት ማሻሻያ ተግባራት ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡

የጤና ሥርዓት ዋነኛ ግብዓት የሆነውን የጤና የሰው ኃብት ልማት እና ዘርፉን እያጋጠሙት ያሉት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ካለፉት በርካታ ዓመታት ወዲህ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እንዳሉ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ይገነዘባል።

በጤና ባለሙያዎች ከሚቀርቡት ጥያቄዎች ባሻገር ሴክተሩ ያሉበት የሥርዐት፣ የአመራር እና የአቅርቦት የመሳሰሉት ችግሮች በርካታ ቢሆኑም እንደ ችግሮቹ ስፋት፣ ጥልቀት እና ውስብስብነት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ከፍሎ ለማየት ማኅበራችን ከጤና ሚኒስቴር እና እህት ማህበራት ጋር ውይይቶች በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እየጠቆመ ይገኛል። የሙያ ማህበራት ተወካዮች የሚሳተፉበት ቀጣይ የውይይት መድረኮችም እንደሚኖሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በዚሁ መሰረት

  1. በጤና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት እየተነሱ ያሉ የጥቅማ ጥቅም፣ደመወዝ፣የሙያ እድገት፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣የትራንስፖርት ችግር፣ የሕክምና ወጭ ሽፋን፣የተጋላጭነትና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የትምህርት እድል፣ ሥልጠናና አቅም ግንባታ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ (conducive working environment) እንዲሁም የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቅ እና ተያያዥ ጥያቄዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ይገነዘባል።
  2. እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ጥያቄዎች በየጊዜ እየተነሱ ያሉ እና በየደረጃው እና ሥርዐት ባለው መልክ ሳይመለሱ የቆዩና እየተጠራቀሙ ያሉ ጥያቄዎች በመሆናቸው ምላሽ ማግኘት እንደሚገባቸው ማህበራችን በፅኑ ያምናል።
  3. በአሁኑ ወቅት በሃገራችን በጤና የሰው ሀብት ልማት ዙሪያ በተለይ በጤና ሙያተኞች ለሚነሱ ጥያቄዎች ወቅታዊ፣ አወንታዊ እና ዘለቄታዊ መፍትሄዎችን መስጠት አስፈላጊ ነው። እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች በርካታ በመሆናቸው በአጭር፣ በመካከለኛና በረጂም ጊዜ ከፋፍሎ ማየት አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።
  4. መሰል ጥያቄዎች በሚነሱበት ወቅት ተገቢውን መፍትሄ ለመስጠት ያመች ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በማድረግ የጋራ መፍትሄዎችን ለማምጣት ጥረት እንዲደረግ እንመክራለን።
  5. በጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎች በሚቀርቡበት ጊዜ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ቀዳሚ በማድረግ እና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ደህንነት እና መብት ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበት እንመክራለን።
    የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር በጤና ሙያተኞች የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ሁሉ የማኅበራችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና አማካሪ ምክር ቤት በኩል ጉዳዩ አፅንኦት ተሰጥቶት አስቸኳይ ምክረ ሃሳብ እንዲቀርብበት ማድረግን ጨምሮ ያላሰለሰ ሙያዊ ድጋፍ የምናደርግ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና አማካሪ ምክር ቤት